በጋሻው ከምድረ ኣውሮፓ*
ጭቆና ሲበዛ ይመራል፣ ነጻነት ስታጣ ያንገበግባል። ንቀት ድንበሩን ሲያልፍ ያበሳጫል፣ በገዛ ሃገር በፍርሃት መኖር ያስመርራል፣ ያለ ጥፋት መታሰር፣ ታስሮ ፍትሕ ማጣት፣ በሃስት ምስክሮችና ዳኞች እድሜ ልክ መታሰር መኖርን ያስጠላል፣ በገዛ ቤት በሰላም መኖር ሲጠፋ ልብ ያደማል።
ህግ ይከበር ሲባል መገደል፣ የሰው ደም ዋጋ ሲያጣ፣ ሰብዓዊ ክብር ሲናቅና ሲዋረድ ትእግስት ያልቃል፣ ለዘመናት ከኖሩበት መሬትና ቄዬ መፈናቀል፣ መባረርና ለማኝ መሆን፣ በኣጠቃላይ በገዛ ሃገር ከሞቱት በላይ ካሉት በታች ሆኖ መኖር ህይዎትና ኑሮ ትርጉም ያጣሉ።
ስለዚህ ነው እንግዲህ ብሶት ሞልቶ ተርፎ ሲፈስ የኦሮሞ ወጣቶች ከዚህ በላይ ግፍንና ጭቆናን መሸከም ኣንችልም በማለት ግፈኞችን ለመጋፈጥ ወደ ኣደባባይ የወጡት። አረሜኔውም ኣገዛዝ ለሰላማዊ የመብት ጥያቄ እንደለመደው የህጻናት ደም በማፍሰሰ ነው መልስ የሰጠው።
ይህ ለኣንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቆም ኣለበት፣ ተባብረን በቃ ልንለው ይገባል። ይህ ግፈኛ ቡድን ስልጣን ከያዘበት 1983 ጀምሮ ሁላችንንም በየተራ ገድሎናል፣ ኣስሮናል፣ ከሃገር እንዲንሰደድ ኣድርጓል። እራሱ ገድሎን ኣሸባሪ፣ ጸረ-ሰላምና ጸረ-እድገት በማለት ድራማ እየሰራብን ኣሹፎብናል። በሃይማኖታችን ሳይቀር ጣልቃ ገብቶ ንጹሃንን በጅምላ ገድሏል። ብዙዎችን ኣስሮ ደብድቦ ኣካለ ስንኩል ኣድርጓል፣ በሺዎች የሚቆጠሩት ዛሬም ታስረው በመሰቃየት ላይ ናቸው። ይህን ሁሉ ለማድረግ የቻለው እኛን በመከፋፈል ነው። ብሄርን ከብሄር፣ ጎሳን ከጎሳ ከፋፍሎን እንደጠላት እንዲንተያይ በማድረግ ነው።
በየተራው በዚህ ጸረ-ህዝብ ቡድን ሲንገደል፣ ሲንፈናቀልና ክብራችን ሲዋረድ ዝምታን መርጠን ቆይተናል። ኣሁንስ ኣልበቃንም? የበቃን መሰለኝ።
እናስ ምን ማድረግ ኣለብን? መልሱ ኣጭርና ቀላል ነው። ኣሁን በኦሮሚያ ና በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል የተጀመረውን የጸረ-ጭቆና ትግል ማቀጣጥልና ከዳር ማድረስ ብቻ ነው። ይህ ግፈኛ ቡድን ካልተወገደ ሰላም ሊኖረን ኣይችልም። ግፈኛው ቡድን ህዝባችንን ሰላም ነስቶ ለሰላምህ ዘብ ቁም እያለ የመብት ታጋዮችን እንዲያወግዝ ሰብስቦ እያሾፈበት ይገኛል።
ትግሉ ተፋፍሞ ዳር እንዲደርስ ሁላችንም በያልንበት የሚፈልግብንን ተግባር መፈጸም ኣለብን። የኣሁኑ የምራችን መሆን ኣለበት።
ለዚህም በመላው የኦሮሚያ ክልልና በኣማራ ክልል የተቀጣጠለው የመብት ትግል ተጥናክሮ መቀጠል ኣለበት። ሌሎች ክልሎችም ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ሰሞኑን ባቀረበው ጥሪ መሰረት የየኣካባቢያቸውን የኣስተዳደር በደል፣ ከመሬታቸው የመፈናቀል፣ የሰባዊ መብት ረገጣዎችን ወዘተ በማንሳት ትግሉን መቀላቀል ኣለባቸው። የጋንቤላ፣ ቤንሻንጉል ደቡብ ኦሞ ህዝቦች በግፍ ለዘመናት ከኖሩበት መሬታቸው ተፈናቅለውና ለዘመናት ጠብቀው ያቆዩት ደኖቻቸውና የተፈጥሮ ሃብቶቻቸው በውጭና በውስጥ የስራቱ ኣገልጋዮች ተወርሶ እነሱ በገዛ ሃገራቸው ስደተኛ ሆነዋል። የኢትይዽያ ሱማሌ ወገኖቻችን በእብሪተኛው ኣሸባሪ መንግስታዊ የማፊያ ቡድን ከቤቱ ጋር የተቃጠለበት ጊዜ ሩቅ ኣይደለም። በኣጠቃላይ በዚህ ማፊያ ቡድን ብሄር ብሄረሰቦችና ጎሳዎች ብቻ ሳይሆኑ እያንዳንዱ ቤተሰብ ስቃይ መከራውን ኣይቷል። በመሆኑም እነዚህንና ሌሎችንም አስተዳደራዊ በደሎችን በማንሳት ትግሉን መቀላቀል ኣለባቸው።
በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ዜጎች በሙሉ ከኦሮሞ ወጣቶች ጎን የሚቆሙ መሆናቸውን በተለያየ መንገድ መግለጽና ትግሉን መቀላቀል። ስብሰባ ሲጠራ ኣለመውጣት፣ በየኣካባቢው ላሉት የኣምባገነኑ ተላላኪዎች ኣለመታዘዝ፣ የኣንድ ለኣምስት ጥርነፋን ማፍረስና ትእዛዛቸውን ኣለመቀበል፣ ልጆቻቸው በትምህርት ቤቶቻቸው የሚያደርጉትን ተቃውሞ ለማስቆም የሚሄዱትን የመንግስት ታጣቂዎችን ልጆቻችን መነካት የለባቸውም ብሎ ከልጆቻቸው ጎን መቆም፣ በቤተ-ክርስቲያንና መስግዶች በጸረ-ህዝብ ታጣቂዎች ለተገደሉት ጸሎት ማድረግ፣ የመብት ጥያቄ በሰላማዊ መንግድ ያቀረቡትን መግድል ይቁም በማለት ማውገዝና የሃይማኖታቸውን ግዴታ መፈጸም።
በመላው ሃገሪቷ የሚገኙና በየደረጃው ያሉት ትምህርት ቤቶች፣ ኮለጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የትግራይ ክልልን ጨምሮ ከኦሮሞ ተማሪዎች ጎን መቆማቸውን በይፋ በመግለጽ ኣምባገንኑን መንግስት ለማስወግድ ትግሉን መቀላቀል።
የኣዲስ ኣበባ ነዋሪዎች የልጆቻቸውን ገዳዮች ሳይሆኑ ለሃገሪቱ ህዝቦች ሰላምና ነጻነት በመቆም ውድ ህይዎታቸን የከፈሉትንና እየከፈሉ ያሉትን የኦሮሞ ተማሪዎችንና ለመብታቸው የተፋለሙትን እንዲያወግዙ እየተገደዱ መሆናቸውን እየየንና እየሰማን ነው። ይህ በእውነቱ ትልቅ ድፍረትና ንቀት ነው። ይህ በተደጋጋሚ እየተፈጸመ መሆኑን መላው የኣዲስ ኣበባ ነዋሪ ያውቃል። ከምርጫ 97 በኋላ እንደዚሁ እንደዛሬ መንግስታዊው ቡድን ያሰማራቸው ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች በየመንደራቸው ሲጫወቱ የነበሩ ህጻናት ሳይቀሩ ግድለው ህዝቡ ወጥቶ የሞቱ ልጆቹን እንዲያወግዝ ተደርጓል። ስለዚህ የኣዲስ ኣበባ ነዋሪ፣ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ሰራተኞች በየበኩላቸው ከዚህ ኣይነት ውርደት ለመላቀቅ በዚህ መንግስታዊ ኣሸባሪ ቡድን ላይ መነሳትና ማመጽ ኣለባቸው።
ለዚህም የመጀመሪያው እርምጃ ኣሸባሪው መንግስት የሚጠራውን ስብሰባ ኣለመውጣት፣ ተማሪዎች የወገኖቻቸውን መገደል በመቃወም ድምጻቸውን ማሰማት። መምህራን የተማሪዎችን በገፍ መገደል በመቃውም የስራ ማቆም ኣድማ ማድረግ፣ የፋብሪካና የመንግስት ሰራተኞችም በያሉበት መንግስታዊ ሽብር ይቁም፣ ገዳዮች ለፍርድ ይቅረቡ፣ የመሬት ወረራና ህዝብን ማፈናቀል ይቆም በማለት ድምጻቸውን ማሰማት ይኖርባቸዋል። ይህ ትግል የሁሉም መብት እንዲከበርና በሃገራችን እንደ የኣለም ህዝቦች ነጽነታችን ተከብሮ እንድንኖር በመሆኑ ሁሉንም የሚመልከት እንጂ የኦሮሞ ወይንም የኣማራ ህዝቦች ጉዳይ ብቻ ኣለምሆኑን ተገንዝቦ ትግሉን መቀላቀልና ይህንን ግፍኛና ነፍሰ ገዳይ ስርዓት ማስወገድ ኣለብን ከዚሁ ጎን ለጎን ኣሸባሪው መንግስታዊ ቡድን የነጻነት ትግላችንን ለማጨናገፍ የሚያደርጋቸውን የተለመዱ መሰሪ ስራዎችን ኣስቀድመን በመከታተል ማጋለጥ ኣለብን። ሁሉም እንደሚያውቀው ይህ ኣሸባሪ መንግስታዊው ቡድን በተልያዩ ጊዜያት የህዝቡን ኣስተሳሰብ ለመቀየር ድራማዎችን በመስራት የታወቀ ነው። ኣከልዳማንና ጂሃዳዊ ሃረካትን የቅርብ ጊዜ ድራማዎች እናስታውሳለን። ኣሁንም በተለይም ካለፈው ኣንድ ኣመት ጊዜ ጀምሮ የኣዲስ ኣበባ ማስተር ፕላን የኦሮሞን ኣርሶ ኣደር ከኖረበት ለማፈናቀል የታቀደውን በመቃወም የኦሮሞ ህዝብ የሚያካሄደውን የመብት ፍልሚያ “የኣሸባሪዎችና ጸረ-ሰላም ሃይሎች” ሴራ ነው እያለ ድራማ ለመስራት እየተጣደፈ መሆኑን ማወቅና ለመልስ ምቱ መዘጋጀት ያስፈልጋል። ለዚህም በተለያየ ጊዜ እራሱ በኣዲስ ኣበባ፣ በሃረርና ድሬደዋ፣ በሃዋሳና በኣምቦ ያቃጠላቸውን የዜጎች ንብረት ምስል እያሰባሰበ ኣሸባሪዎች ኣቃጠሉ ብሎ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ነው። በሃገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ተደራጅተው የሚታገሉትን የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን ገዢው ኣሸባሪ መንግስታዊ ቡድን በኣሸባሪነት ከፈረጃቸው ተቃዋሚዎች ጋር በማገናኘት ወደ እስር ቤት ለማጋዝ በመጣደፍ ላይ እንደሚግኝ ጥርጥር የለውም።
ይህ እንዳይሆን ትግላችንን በየፈርጁ በማፋፋም ኣሸባሪውን መንግስታዊ ቡድን ፋታ መንሳት ያስፈልጋል። ሁለት ሞት የለም። ጥቂቶች በቁም ገድለውናል። ለዚህ ቡድን ኣንገታችንን ከዚህ በላይ መስጠት የለብንም።
የኣዲስ ኣበባ ወጣቶች እምቢ ለሃገሬ፣ ኣሻፈረኝ በሉ። ፋኖ ተሰማራ እንደገና መዘመር ኣለበት። በርካታ ወጣቶች የተሰማቸውን በመናገራቸውና በመጽፋቸው ታስረዋል፣ በጨካኞች የብረት ኣለንጋ ተገርፈዋል፣ ዛሬም እየተገረፉ ናቸው። ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በማድረጋቸውና በህዝብ በመመረጣቸው፣ ህዝቡ ድምጼን በጉልበተኞች ኣልቀማም ብሎ በመሰለፉ ምክንያት ኣዛውንቶችና ታላላቅ የሀገሪቱ ሊቆች ተደብድበው በእስር ቤት እንደተቀለደባቸው የማትረሱት ነው 1997።
ይሄው ዛሬም ኣዛውንት ኣርሶ ኣደሮች፣ እናቶችና ህጻናት ሳይቀሩ በጨካኙ መንግስታዊ ኣሸባሪ ቡድን እየተገደሉና በፌሮ ብረት እየተጨፈጨፉ ይገኛሉ። ታዲያ ከዚህ በላይ ውርደት፣ ከዚህ በላይ ንቀት ኣለ። የኣዲስ ኣበባ ወጣቶች ማወቅ ያለባችሁ በኣሁኑ ጊዜ በየሰፈሩ እናንተንም ሆነ ቤተሰቦቻችሁን በስብሰባ ወጥረው የያዙት እናንተ የመብትና የነጻነት ትግሉን እንዳትቀላቀሉ በመፍራት መሆኑን ነው። በኣዲስ ኣበባ ረብሻ የለም ሰልፍም ኣይካሄድም እና በሰብሰባ ህዝቡን ማዋከቡ የናንተ ፍራቻ መሆኑን እወቁ። የገዢው ቡድን ለህያ ኣምስት ኣመታት ኣታሎሀል ከዚህ በላይ ሊታታልለን ኣትችልም በሉ፣ ተነሱ፣ የመብት ታጋዮች ኣሸባሪ እየተባሉ ገዳዩና ኣሸባሪው መንግስታዊ ቡድን የሚንግረን ስለ ሰላም፣ ስለ ልማትም ሆነ እድገት የሚንሰማበት ጊዜ ኣብቅቷል። ሰላም እየነሱ ስለ ሰላም ማውራት፣ 15 ሚሊዮን ህዝብ በረሃብ እየተሰቃዬና በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት በምግብ እጦት በእናታቸው እቅፍ እየረገፉ እያየንና እየሰማን በባዶ የልማት ፕሮፓጋንዳ መታለልና ከትግሉ ወደኋላ ማፈግፈግ ከወንበዴው ና ኣሸባሪው የእኔ ሃይሌ ማሪያም ደሳለኝና ኣባይ ጸሃዬ ቡድን ደጋፊ ከመሆን ውጭ ሌላ ትርጉም ኣይኖረውም።
ብሶት የወለደው ህዝባዊ የመብት ትግል ተጠናክሮ መቀጠል ኣለበት።
ክብርና ምሥጋና ለህዝባቸው ነጻነትና ክብር ህይዎታቸውን ላጡ፣ በጨካኞች ተደብደበው ኣካላቸው ለጎደለ፣ በእስር ቤቶች መከራና ሲቃይ እየተፈራረቀባቸው ላሉት ጀግኖች የኦሮሞ ልጆች፣
ክብርና ምስጋና በሰሜን፣ በደቡብ በምስራቅና በምእራብ ለነጻነታቸው ስታገሉ መከራን ለተቀበሉ ሁሉ።
የተባበረና ብሶት የወለደው ህዝባዊ ትግል ያሸንፋል።